የግብፅ ብሔራዊ ቡድን በነገው የኢትዮጵያ ጨዋታ ወሳኝ ተጨዋቾቹን ወደ ቋሚ አሰላለፍ ሊያካትት እንደሚችል ተገልጿል። አሰልጣኝ ሆሳም ሀሰን ብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ጨዋታውን ሲያደርግ ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ የበርካታ ተጨዋቾች ለውጥ ለማድረግ ማሰባቸው ተነግሯል።
በጨዋታው የቡድኑ ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂ የአል አህሊው መሐመድ ኤል ሼናዊ ወደ ቋሚ አሰላለፍ ሊመለስ እንደሚችል ተገልጿል። በተጨማሪም አሰልጣኝ ሆሳም ሀሰን የሊቨርፑሉን ተጨዋች መሐመድ ሳላህ በቋሚነት ያሰልፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የፈርዖኖቹ ቋሚ አሰላለፍ ምን ሊመስል ይችላል?
- ግብ ጠባቂ: – መሐመድ ኤል ሼናዊ
- የኋላ መስመር: – መሐመድ ሀኒ፣ ራሚ ራቢያ፣ መሐመድ አብደልምኔም፣ አህመድ ነቢል ኮውካ
- የመሐል ሜዳ: – ማርዋን አትያ፣ ሀምዲ ፋቲ፣ ማህሙድ ሳቤር፣ ትሪዝጌት
- የፊት መስመር: – መሐመድ ሳላህ፣ ሙስጠፋ መሐመድ፣ ዑመር መርሙሽ
ፈርዖኖቹ ትላንት ምሽት በሞሮኮ የግብፅ አምባሳደር በተገኙበት ጨዋታው በሚደረግበት ስታዲየም የመጀመሪያ ልምምዳቸውን ሰርተዋል። ዋልያዎቹ በበኩላቸው ትላንት ሌሊት 6:00 ሰዓት በሞሮኮ የመጀመሪያ ልምምዳቸውን መስራት ችለዋል።
የግብፅን ብሔራዊ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ በዘጠና ደቂቃ የነጥብ ጨዋታ ያሸነፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነው።