ትናንት ምሽት በአሜሪካ የጀመረው የክለቦች ዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ እንደ ታላላቅ ክለቦች ሁሉ አነስተኛ ቡድኖችም እየተሳተፉ ነው። ከእነዚህ አነስተኛ ቡድኖች መካከል 5,000 ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው ሜዳ ያለው የኒውዚላንዱ ክለብ ኦክላንድ ሲቲ አንዱ ነው።
የኦሺያ ሻምፒዮን የሆነው ኦክላንድ ሲቲ ዛሬ ምሽት የጀርመኑን ታላቅ ክለብ ባየር ሙኒክን ይገጥማል። ክለቡ ወደ ክለቦች ዓለም ዋንጫ ውድድር ሲጓዝ ያወጣው ወጪ በአመት ከሚያገኘው ገቢ በሁለት እጥፍ የሚበልጥ እንደሆነ ተነግሯል።
የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች እና የሚመኩበት የፊት መስመር አጥቂያቸው አንጉስ ኪልኮሊ በሙሉ ሰዓቱ የቁሳቁስ ተቋም ማናጀር እንደሆነ ተገልጿል። እግር ኳስን በትርፍ ጊዜው እንደሚጫወት ያስረዳው አጥቂው፣ “ውሎዬ ሰዎች እና ሽያጭ መቆጣጠር ነው፣ ከስራ በኋላ ወደ ልምምድ እሄዳለሁ” ብሏል።
አብዛኞቹ የክለቡ ተጫዋቾች የስራ እረፍት ባለማግኘታቸው ይህን ጉዞ ለማድረግ እንዳልቻሉ ተዘግቧል። በተጨማሪም የቡድኑ ግብ ጠባቂ ኮነር ትራሴይ በሙሉ ሰዓቱ የመጋዘን ጠባቂነት ስራ ላይ ተሰማርቶ እንደሚሰራ ተገልጿል።