የቀድሞ የሊቨርፑል አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ የቡድኑ ደጋፊዎች በአሌክሳንደር አርኖልድ ላይ ያሰሙት የተቃውሞ ድምፅ እንዳበሳጫቸው ገልጸዋል።
አርኖልድ ሊቨርፑልን እንደሚለቅ ካሳወቀ በኋላ በነበረው ጨዋታ፣ በእያንዳንዱ የኳስ ንክኪው ከደጋፊው የተቃውሞ ጩኸት ሲሰማ ነበር።
የሊቨርፑል ፋውንዴሽን የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት ክሎፕ፣ “ምን ማሰብ እንዳለባችሁ ልነግራችሁ አልችልም፤ ነገር ግን ያሰባችሁት ስህተት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
“በአርኖልድ መልቀቅ አትበሳጩ እያልኩ አይደለም” ያሉት የርገን ክሎፕ፣ ነገር ግን እሱ ለሊቨርፑል ያደረገውን ነገር መርሳት የለባችሁም ብለዋል።
አክለውም “የጩኸት ድምፁን ስሰማ ቴሌቪዥኑን ነው ያጠፋሁት፤ በጣም አበሳጭቶኝ ነበር። የተደረገው ነገር እኛን አይወክልም” ሲሉ ክሎፕ ተናግረዋል።
አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ነገ እሁድ በአንፊልድ ስታዲየም ተገኝተው የሊቨርፑልን የሊግ ዋንጫ ድል ያከብራሉ።